News

ሰክሰስ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም የብድር አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገለጸ

ሰክሰስ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም የብድር አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገለጸ ታህሳስ 21/2017(አሐዱ ሬዲዮ) ሰክሰስ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አክሲዮን ማህበር የባለአክሲዮኖችን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት በጊዮን ሆቴል አካሂዷል። አክሲዮኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አነስተኛ የፋይናንስ ሥራ አዋጅ መሠረት በ2016 ሕጋዊ እውቅና ማግኘቱን የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ሀይሉ ገልጸዋል። የተቋሙ ዋና አላማ የብድር አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ሲሆን፤ ማህበሩ ከተመሠረተ ጀምሮም ለበርካታ ደንበኞች የተለያዩ የዋሥትና እና 8 አይነት የብድር አገልግሎቶችን እየሠጠ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። በ77 ሚሊዮን 800 ሺሔ የተፈረመ ካፒታል ሥራ የጀመረው አክሲዮኑ እስካሁን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የሠጠ ሲሆን፤ ተጨማሪ 10 ቅርንጫፎችን ለመክፈት ጥናት አካሂዶ 4ቱን ቅርንጫፎች በቅርቡ ለማሥጀመር የሠራተኞች ቅጥር አውጥቷል ተብሏል። በዕለቱ በ3 አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው ማህበሩ፤ በቀጣይ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ተማሪዎች እና አካል ጉዳተኞች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አስረድቷል።